Clergy

የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ዲያቆናት

እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጆችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የገባው ቃል ኪዳን በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ፣ ብቸኛና ፍጹም በሆነ ክህነቱ መስዋዕት አቅራቢ ካህን፣ መስዋዕት ተቀባይ አምላክ፣ ራሱም እውነተኛ መስዋዕት በመሆን አዳነን፤ ከበሽታችን ፈወሰን፤ ሞታችንን ሞቶ የትንሣኤ ሕይወትን ሰጠን። በዚህም አጥተነው የነበረው ጸጋችን ተመለሰልን፣ አዲስ ሕይወትም ተሰጠን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የፈጸመው የማዳን ሥራ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ላሉ ምዕመናን እንዲደርስ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተልን። እነዚህን ምሥጢራት በክርስቶስ ክህነት የሚፈጽሙ አባቶች በአንብሮተ ዕድ፣ በንፍሐተ መንፈስ ቅዱስ ሾመልን። ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ እንዲህም አላቸው ”መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም” እንዲል። ዮሐ. ፳፡ ፳፪-፳፫። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም። የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ” (ማቴ ፲፮፥፲፰) ብሎ ስልጣነ ክህነትን ሰጠው። ኃላፊነቱንም እንዲህ በማለት አደራ አስረከበው፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታዬ ሆይ፥ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” ጌታችን ኢየሱስም “በጎቼን ጠብቅ አለው”። ዳግመኛም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” “ጠቦቶቼን አሰማራ አለው።” ሦስተኛ ጊዜም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?” አለው። ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን? ስላለው ተከዘ። “ጌታዬ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።” “እንኪያስ ግልገሎቼን ጠብቅ አለው።” ዮሐ. ፳፩ ፦ ፲፭ – ፲፯። በጎች የተባሉ ለጊዜው ሀዋርያት ሲሆኑ ፍጻሜው ግን መላው መምህራንን ጠብቅ ማለቱ ነው። ጠቦቶች የተባሉ ለጊዜው ሰባ ሁለቱ አርድዕት ሲሆኑ ፍጻሜው ግን መላውን ጠብቅ ማለቱ ነው። ግልገሎች የተባሉ ለጊዜው ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ሲሆኑ ፍጻሜው ግን መላውን ጠብቅ ማለቱ ነው።

የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መስዋዕት አድርጎ በማቅረቡ የክህነት አገልግሎት ዋና ይዘት ፍቅር፣ ራስን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፎ መስጠት መሆኑን አሳየን። ከጌታችን የባሕርይ ምንጭነት የተገኘው የአዲስ ኪዳን ክህነት ሐዋርያትን አረስርሶና አርክቶ በቂ የሆነ ክህነታዊ ተግባርም አሳይቶ አሁን ባሉ አባቶች ላይ ይገኛል። አምላካቸውን ያገኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽማቸው ምሥጢራት ስላሏት፣ ምሥጢራቱ የሚፈጸሙትም የግድ በካህናት ስለሆነ ክህነት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ አስፈላጊና የማይቀር ነው። ይህም በዓለም ያለው በእግዚአብሔር አርዓያና ምሳሌ የተፈጠረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን እንዲያይበትና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝበት ነው።

አባታችን መላከ ጽዮን ቀሲስ ጌቱ ረጋሳ የቤተክርስቲያናችን አስተዳዳሪና ካህን ሁነው ቁጠራቸው አነሰ ፤ ቦታው አይመችም ሳይሉ ከምእመኑ ጋር ችግሩንና መከራውን አብረው እየተካፈሉ ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ሰዓት በሙሉ አገልግሎት ለመስጠት ዋነኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።እግዚአብሄር ረጂም እድሜና ጤና ይስጥልን እንላለን፤

ለእግዚአብሄር ክብር ምስጋና ይግባውና ቤተክርስቲያናችን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም በአንድ ካህንና በሰባት ዲያቆናት ሙሉ የሆነ አገልግሎት በመስጠትም ትገኛለች።

በሌላ በኩል ደግሞ በዓመታዊ የንግስ በዓላት ወቅት የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ማትያስ፣የቶሮንቶ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ የኦታዋ መድሃኔአለም ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ የሞንትሪያል መድሃኔአለም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም የኪችነር ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ካህናት እየመጡ ያገለግላሉ።

በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ካህናትና ዲያቆናት በከፊል በፎቶው ላይ የሚታዩት ናቸው።