Worship & Pray

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እና የጸሎት አገልግሎት

እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣው ከተፈጠረበት ሥርዓት ጋር ነው። የዓለም ተፈጥሮም ያለ ሥርዓት ትርጉም የለውም። ፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔርን ከሚያደንቅበት ነገር አንዱ የተሰጠውን ሥርዓት ጠብቆ መጓዙ ነው። ወንዞች ወደ ዝቅተኛ ስፍራ ይፈስሳሉ፣ አራዊት በሌሊት ይወጣሉ፣ ሰዎች ተግባራቸውን በቀን ያከናውናሉ፣ ፀሐይ በምሥራቅ ትወጣለች። ይህ ሁሉ የሚያስተምረን ሥርዓት ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ የነበረና ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን ነው። መዝ ፩፻፫፡ ፮-፳፭።

ሥርዓት ሠርዐ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ስም ነው። ትርጉሙም ደምብ አሠራር ማለት ነው። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም ስንል የቤተ ክርስቲያን መገልገያ ደንብ ማለታችን ነው። አምልኮተ እግዚአብሔር የሚከናወንባት ቤተ ክርስቲያን ምስጢራዊና መንፈሳዊ ሥርዓት አላት። መንፈሳዊ አገልግሎቷንም የምትፈጽምበት ደንብ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ይባላል። ይህም ደንብ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየጊዜው በሲኖዶስ በመወሰን ለቤተ ክርስቲያን ያስረከቡት ነው። በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ የዕለት ተዕለት ሥርዓተ አምልኮታቸውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመመራት ያከናውናሉ። በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ከሚከናወኑት ውስጥ አንዱ ሥርዓተ ቅዳሴ ሲሆን የበዓላት አከባበርም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሥር ይጠቃለላል።

ቅዳሴ

ቅዳሴ የአንዲቷ አማናዊት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ገጽ እንደሆነ ሁሉ የምእመናን መሰባሰብ ደግሞ የቅዳሴ የመጀመሪያ መሠረት ነው። በመሰባሰብ የሚፈጸመው የቅዳሴ ሥርዓታችን አስቀድሞም በቅዱሳን መላእክት ዓለምም የነበረና በምድር ባለች መቅደሱም በምእመናን መሰባሰብ የሚፈጸም የማህበር ጸሎት ነው። ተሰባስቦ እግዚአብሔርን ማመስገን መሥዋዕትን ማቅረብ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳንም በምሳሌ የቆየ ቢሆንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት ጋር በቤተ አልዓዛር የአይሁድን ፋሲካ ሲያከብር የአማናዊው ቅዳሴ መሠረት ተጣለ። ሉቃ.፳፪፡ ፯። የቤተ እስራኤል ጉባኤ መሠረት ይሆን ዘንድ አሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች የመረጠ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መሠረቶች የሆኑ ሐዋርያትን ሰብስቦ በመንግሥተ ሰማያት ማዕድ ላይ አስቀመጣቸው። ሉቃ.፳፪፡ ፳፱-፴። በዚህም በሐዋርያት በኩል የቤተ ክርስቲያን አንድነት መመሥረቱን እንረዳለን። በመንፈስ ቅዱስ መምጣት የጌታን ምስጢር ሁሉ የተረዱት ሐዋርያት አባቶቻችንም የቅዳሴን ምስጢር ምእመናንን ሰብስበው በአንድነት የሚፈጽሙ ሆነዋል። የሐዋ ፳፡ ፪። ይህ ሥርዓት በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በእርግጥም የጸና ሆኗል።ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁናየሚለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስበመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ…” በማለት በእርሱ ዘመን የምእመናን መሰብሰብ ለዐበይት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ቅድመ ሁኔታ እንደነበረ ይናገራል። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፡ ፲፰። ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና በማለቱም ይህ በሥርዓተ ቅዳሴ በቤተ ክርስቲያን የመሰባሰብ ምስጢር ከዚያ በኋላ ሥርዓቱን ጠብቆ በትውፊት የሚተላለፍ ሆኗል። የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑ አበውም ይህን የሐዋርያት ትውፊት ተቀብለው በቀጥታ ለትውለድ አስተላልፈዋል።

ዘወትር እሁድ ሳምንታዊ የሰንበት አገልግሎት መርሃ ግብር
  • ከንጋቱ ፲፪ ሰዓት (6 AM) እስከ ጥዋቱ ሰዓት (7 AM) የነግህ ኪዳንና ጸሎት የምናደርግበት፤
  • ከጥዋቱ ሰዓት (7 AM) እስከ ሰዓት (8 AM) ካለ ጥምቀተ ክርስትና የምናደርግበት፤
  • ከጥዋቱ ሰዓት (8 AM) እስከ ሰዓት (11 AM) ሥርዓተ ቅዳሴ የምናደርግበት፤
  • ከረፋዱ ሰዓት (11 AM) እስከ ሰዓት ከአስር (11:10 AM) ለዕለቱ የተመረጡ መዝሙሮች በህጻናት መዘምራን የምንዘምርበት፤
  • ከረፋዱ ሰዓት ከአስር (11:10 AM) እስከ ሰዓት ከሃያ (11:20 AM) ተአምረ ማርያም የሚነበብበት፤
  • ከረፋዱ ሰዓት ከሃያ (1120 AM) እስከ ሰዓት ተኩል (11:30 AM) ለዕለቱ የተመረጡ መዝሙሮች በሰ//ቤት መዘምራን የምንዘምርበት፤
  • ከረፋዱ ሰዓት ከአርባ አምስት (11:45 AM) እስከ  ሰዓት ተኩል (12:30 PM) ስብከተ ወንጌልና ቃለ ቡራኬ የሚሰጥበት፤
  • ከረፋዱ ሰዓት (12:30 PM) ተኩል ጀምሮ ለዕለቱ የተዘጋጀ ጸበል ጸዲቅ በአዳራሽ ውስጥ የምንቀምስበት ይሆናል።
በዓላት

በዓላት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን ከምትፈጽምባቸው ሥርዓቶች መካከል እንደ አንዱ ሆነው ይጠቀሳሉ። በበዓላት ምእመናን ረድኤት በረከት ከማግኘታቸው ባለፈ ቤተ ክርስቲያን የምትሰጣቸውን አገልግሎቶች የሚቀበሉባቸው መንፈሳዊ መድረኮች ናቸው። በበዓላቱ መምህራን ትምህርተ ወንጌልን ለምእመናን ያደርሳሉ። በበዓላት አከባበር ሥርዓት ውስጥ ምእመናን በቤታቸው፤ በአካባቢያቸውና በአደባባይ ሁሉም በጋራ በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና ጌትነት፣ ለሰውም ያደረገውን የማዳን ሥራ የሚመሰክሩበት፣ በቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ላይ ያላቸውን ጽናት ለየትኛውም ወገን ያለሀፍረት የሚገልጹበት የአገልግሎት ዕድል ነው።

ጌታችንበሰው ፊት የሚመሰክርልኝን እኔም በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” /ሉቃ ፲፪፡ / ያለውን ቃሉን በማክበርና በመጠበቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅና በአደባባይ የምታከብራቸው ማራኪ በዓላት አሏት። እነዚህ በዓላት በዓይነታቸው ሁሉንም የክርስቲያን ቤተሰብ በየመዓርጉ፣ በየጸጋው እንደየአቅሙ የሚያሳትፉ በመሆናቸው ደማቅ ናቸው። በተለይ የጌታችን የመድኀኒትችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ፣ ተአምራትና የማዳን ነገር የሚዘክሩትን በዓላት /በዓለ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ መስቀል/ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ቀን ቀመር መሠረትም ብሔራዊ በዓላት እንዲሆኑ በሕግ ተመዝግበው የሚታወቁና ደምቀው የሚከበሩ ናቸው። እነዚህ ወንጌልን መሠረት ያደረጉ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥና በምእመናን ልብ ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቷቸው መገኘቱ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ ለስብከተ ወንጌል የሰጠችውን የማያቋርጥ ትኩረት ይመሰክራል። ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ሕይወቷም አገልግሎቷም ነውና እንዲህም ሆኖ እስከዚህ ዘመን ደርሷል።

ከላይ በተጠቀሱት የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትውፊቶች መሰረት የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንም ለኦታዋና ጋቲኖ አካባቢ ለሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች አገልግሎቷን በመስጠት ላይ ትገኛለች። በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የሚሰጡት የተለያዩ የጸሎትና የበዓላት አከባበር አገልግሎቶች እንዲሁም አገልግሎቶቹ የሚሰጡባቸው ቀናትና ሰዓት ከዚህ በታች በዝርዝር ተመልክቷል። እርስዎም በተጠቀሱት ጊዜያት ቤተክርስቲያን በመገኘት የአገልግሎቶቹ ተሳታፊ በመሆን ለነፍስዎ የሚሆነውን ስንቅ ያገኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።

ወርሃዊ የእመቤታችን በዓል አገልግሎቶች መርሃ ግብር

እነዚህ በዓላት ለዕለቱ በሚቀርበው እሁድ ይከበራሉ።

ዓመታዊ የእመቤታችን በዓል አገልግሎቶች መርሃ ግብር

የሰኔ ማርያም፡ የመስከረም ማርያም ፡የህዳር ጽዮንና ፡የጥር ማርያም  በዕለቱም እንዲሁም ለዕለቱ በሚቀርበው መጪ እሁድ ይከበራሉ።

ማሳሰቢያ 

በዚህ መርሃ ግብር የቀናትና የሰዓት ለውጦች ካሉ ቤተክርስቲያኗ ለምእመናን በጊዜው የምታሳውቅ ይሆናል፡፡

ዓመታዊ የዳመራ በዓል አገልግሎት መርሃ ግብር

መስከረም ፲፮ ቀን በዋለ በሚቀርበው እሁድ ከቀኑ ሰዓት (3 PM) እስከ ምሽቱ ፲፪ ሰዓት (6 PM) በቤተክርስቲያናችን ቅጥር ግቢ ውስጥ ይከበራል

ዓመታዊ የልደትና የትንሣኤ በዓላት አገልግሎቶች መርሃ ግብር
  • ከምሽቱ ፬ ሰዓት (10 PM) እስከ ሌሊቱ ፮ ሰዓት (12 AM) ስብከተ ወንጌል፣ መዝሙርና ኪዳን፤
  • ከሌሊቱ ፮ ሰዓት (12 AM) እስከ ፰ ሰዓት ተኩል (2:30 AM) ሥርዓተ ቅዳሴ፤
  • ከሌሊቱ ፰ ሰዓት ተኩል (2:30 AM) እስከ ፱ ሰዓት (3 AM) ጸሎትና ቃለ ቡራኬ፤
  • ከሌሊቱ ፱ ሰዓት (3 AM) ጀምሮ ለዕለቱ የተዘጋጀው ጸበል ጸዲቅ ይቀርባል።
ዓመታዊ የፍልሰታ ጾም አገልግሎት መርሃ ግብር

ከነሐሴ እስከ ፲፮ የቅደሴ አገልግሎት በአባቶች መርሓ ግብር፤ 

  • ከረፋዱ ሰዓት (10 AM) እስከ ፲፪ ሰዓት (6 PM) የነግህ ኪዳንና የውዳሴ ማርያም ትርጉም፤
  • ከቀኑ ሰዓት (12 PM) እስከ ሰዓት (3 PM) ቅዳሴ፤
  • ከቀኑ ሰዓት (3 PM) ጀምሮ ለዕለቱ የተዘጋጀ ጸበል ጸዲቅ በአዳራሽ ውስጥ ይቀርባል።

ማሳሰቢያ 

በዚህ በፍልሰታ መርሃ ግብር ቀናትና የሰዓት ለውጦች ካሉ ቤተክርስቲያኗ ለምእመናን በጊዜው የምታሳውቅ ይሆናል፡፡

የነቢያት ጾም፤ ዓቢይ ጾምና፤ የሰሙነ ሕማማት አገልግሎት መርሃ ግብር

ዘወትር ሰኞ፣ ዕረቡና አርብ፡ ከምሽቱ ሰዓት (9:00 PM) ጀምሮ የዘወትር ጸሎት በዙም በቀጥታ የሚደረግ ይሆናል።

ማሳሰቢያ 

በዚህ መርሃ ግብር የቀናትና የሰዓት ለውጦች ካሉ ቤተክርስቲያኗ ለምእመናን በጊዜው የምታሳውቅ ይሆናል፡፡


ሚያዝያ 2020