Church History – (Tinte Tarik)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በጥቂቱ

ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር የምስጢር ሀገር ናት፡፡ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» (መዝ. ፷፯፥፴፩) ተብሎ እንደተነገረላት በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን እንደ ማዕዘን ድንጋይ የሚታዩ ታቦተ ጽዮን እና ግማደ መስቀሉን እጆቿን ዘርግታ ተቀብላለች፡፡ ከሌሎች ክፍለ ዓለማትም ተለይታ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን እምነት አሻራ በጉልህ ይንጸባረቅባታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከስድስቱ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክሪስቲያናት ማለትም ከኮፕት (ግብጽ)፣ ህንድ፣ ሶርያ፣ አርመንና ኤርትራ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ከ፵ ጊዜ በላይ የተነሳች ሲሆን ከክርስትና በፊት የብሉይ ኪዳንን እምነትና ባህል ተቀብላ እግዚአብሔርን ታመልክ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ለአብነት ያህል ጥቂቱን አቅርበን ወደ አዲስ ኪዳን ዘመን እንሸጋገራለን።

የንግስተ ሳባ ንጉስ ሰሎሞንን መጎብኘት

የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና፣ የእግዚአብሔርንም ስም በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቶና ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ ነገረችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት። (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ፲፥፩-፲፫፤ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ፱፥፩-፲፪) ንግስተ ሳባ ከሰሎሞን ምኒልክ የሚባል ልጅ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ወለደች፣ ልጁም አድጎ የአባቱን ሀገር ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶ ሲመለስ የሙሴን ጽላትና ካህናተ ኦሪትን፣ እንዲሁም አያሌ የብሉይ መጻሕፍትን ከሊቆቻቸው ጋር ይዞ መጣ (አባ ጎርጎርዮስ ፲፱፻፺፱) ንግስተ ሳባ በኢትዮጵያ የነገሰችው ከክርቶስ ልደት በፊት ... ከ፲፻፲፫ እስከ ፱፻፹፪ .. ነበር። እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ጽላት ዛሬ በርዕሰ አድባራት አክሱም ፅዮን ቤተ ክርስቲያን ይገኛል።

የንግስተ ሳባ ንጉስ ሰሎሞንን መጎብኘት
የኢትዮጵያ ንጉሥ ባዜን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ከገበሩለት ሦስት ነገሥታት አንዱ ስለመሆኑ

ነቢዩ ዳዊትኢትዮጵያውያን በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐመድ ይቅማሉ፤ የጠርሲስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታ ያመጣሉ፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታትም እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታልብሎ (መዝ. ፸፩፥ -) በተናገረው ትንቢት መሠረት ሄሮድስ በነገሠበት ዘመን የይሁዳ ክፍል በምትሆን በቤተልሔም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ጥበበኞች ሰዎች ከምሥራቅ መጡ፤ ወደ ቤት ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ጋር አይተው ከፈረስ ሠረገላ ወርደው ሰገዱለት፤ ሳጥናቸውን ከፍተው ኮረጁዋቸውን ፈትተው ወርቁን ዕጣኑንና ከርቤውን ግብር አገቡለትብሎ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ.፪፥፩-፲፩) እንደጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ተወልዶ ሳለ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ከገበሩለት ሦስት ነገሥታት አንዱ የኢትዮጵያ ንጉሥ ባዜን እንደነበረ ይተረካል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስየግመሎች ብዛት፣ የምድያምና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፤ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ” (ኢሳ.፷፥፮) ብሎ በትንቢት እንደተናገረው የወርቅ እጅ መንሻ ያቀረበው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ እንደነበር ይነገራል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ክርስቶስን ያወቀችውና መባ በማቅረብ ልደቱን ያከበረችው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መባሉዋ ትክክል ነው። ማጣቀሻ(http://www.eotc-patriarch.org/)ይመልከቱ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ከገበሩለት ሦስት ነገሥታት አንዱ ስለመሆኑ
የኢትዮጵያ ንግሥት ህንደኬ አዛዥና ጃንደረባ ባኮስ የኢየሩሳሌም የአምልኮ ጉዞና ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ ስለማምጣቱ

የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደሆነ መንገድ ሂድ አለው፤ ተነሥቶም ሔደ፤ እነሆምህንደኬየተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቡዋም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፤ መንፈስም ፊልጶስን ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፤ ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማናበእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው፤ እርሱምየተረጐመልኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” አለው፤ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፤ ያነብበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፥ እንደ በግ ወደመታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፤ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራልጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ እባክህ ነቢዩ ይህን ስለማን ይናገራል ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ አለው፤ ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሔዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም እነሆ ውሀ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው?” አለው፡፡ ፊልጶስምበፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአልአለው፤ መልሶምኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁአለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፤ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውሀ ወረዱ፤ አጠመቀውም፤ ከውሀውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና” (የሐዋ. . ፰፡፳፮-፴፱) በማለት ወንጌላዊው ሉቃስ እንደተረከው የክርስትና እምነትና ጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ፴፬ .. በኢትዮጵያ ንግሥት በሕንደኬ ጃንደረባ በባኮስ አማካይነት ነው፡፡ ያጠመቀውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወንጌላዊው ፊልጶስ ነው፤ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ" የሚለውን የእምነት ቀመር በመናገር የጀመረና ለዓለም ያበረከተ ኢትዮጵያዊው ባኮስ ነው፡፡

ምስል 1 ና 2 -ባኮስ ኢየሱስ ክርስቶስ

የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አውቆና አምኖ በማሳመን ለወገኖቹ ትክክለኛውን እምነት ስለ ሰበከ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ "ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ታምናለች፣ ትሰብካለች፤ ታሳምናለች፡፡ በዘመነ ሐዋርያት የክርስትና እምነትን በመቀበል የመጀመሪያው የወንጌል አዝመራ የሆነው ባኮስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የእምነትና ሥርዐተ አምልኮ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ነው፡፡ ለሐዲስ ኪዳን ኢትዮጵያም ዓለም ዐቀፍ እውቅና ያገኘ የቤተ ክርስቲያናችን መሥራች ነው፡፡ ባኮስ በዚህ ሃይማኖታዊ ጒዞው የሕገ ኦሪትንና የሕገ ወንጌልን ጽድቅ በአንድ ጒዞ በመፈጸም የራሱንና የአገሩን ስም በቅዱስ መጽሐፍ ለማስጠራት በቅቷል፡፡ ባኮስ ወደ አገሩ ተመልሶ ከቅዱስ ፊልጶስ ስለ ክርስቶስ የሰማውንና የተረዳውን ለወገኖቹ ኢትዮጵያውያን እንደ አስተማረ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሓፊ አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ጽፎአል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችውም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ፊልጶስ የክርስትና አባቷ ስለሆነ በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንፃ ጽላት ቀርፃ ታከብረዋለች፡፡ በጸሎቱና በአማላጅነቱም ትታመናለች፤ ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ናትናኤል፣ ቅዱስ በርተሎሜዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ በኑብያና በኢትዮጵያ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ወንጌልን እንደ ሰበኩ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች እነሩፊኖስና እነ ሶቅራጥስ መስክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት መስፋፋት

በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት እንዲስፋፋ ጉልህ አስተዋጽዖ ካበረከቱ ቅዱሳን መካከል ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ቅዱስ ላልይበላ፣ ተሰዓቱ ቅዱሳን እና አቡነ ተክለ ኃይማኖትን በዚህ እትም በአጭሩ እናስተዋውቃለን።

ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ

4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን "ቅዱስና ያለ ተንኰል የሚኖር ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል" (ዕብ.፯፣፳፮) ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት እንደተናገረው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሾማቸው ከሐዋርያት ሐረገ ክህነት ተያይዞ የመጣ የሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባኛል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ላከች፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክም ራሱኑ ሾሞ ላከው፡፡ ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በመጀመሪያው ምዕት ዓመት ይሁን እንጂ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር የተሰጣት በአራተኛው ምዕት ዓመት በ፫፻፴ .. ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተልኮ ሔዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት በዐዋጅ ተሰብኳል፡፡ ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ፡፡ በዚሁ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንታዊት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሥርዐተ እምነት አንድነትና የእህትማማችነት ህብረት ስለነበራት ግብፃውያን ጳጳሳት ሥልጣነ ክህነት በመስጠት ብቻ ተወስነው የቀረው የአስተዳደሩና የውስጥ አመራሩ ይዞታ ግን በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይካሄድ ነበር፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በሥርዐተ ትምህርትና በባህል ራሱን የቻለ አቋም የነበራትና ያላት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ

ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ ቀን ፭፻፶፭ . በአከሱም ከተማ ተወለደ፤ ዜማውንም ከ፭፻፵-፭፻፷ . አዘጋጀ፤ ግንቦት ፲፩ ቀን ፭፻፸፩ . በሰሜን ተራራዎች በጸለምት ዋሻ ውስጥ ተሠወረ፡፡ ቅዱስ ያሬድ የግእዝ፣ እዝልና አራራይ ዜማዎችን ከሦስት ወፎች /መላእክት በወፎች ተመስለው/ መማሩን ሊቃውንት ይገልጣሉ፡፡ እነዚህ መላእክት እየመሩት ወደ አርአያም አርጎ የ፳፬ቱን ካህናተ ሰማይ ዜማ ከተማረ በኋላ ጠዋት በ፫ ሰዓት በአክሱም ቤተ ክርስቲያንሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አረአዮ ለሙሴ ዘከመ ይግበር ግብራ ለደብተራብሎ አዜመ፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያ ዜማውአርያምበመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም ሌላ በትምህርት ሂደትም አስተዋጽዖ አድርጓል፤ የድጓን፣ የጾመ ድጓን የዝማሬ መዋሥዕትንና የቅዳሴን ትምህርት ከማስተማሩም በላይ ለቅኔ ትምህርትም መሠረት ጥሏል፡፡ ዜማውን ካዘጋጀ በኋላ ለ፲፩ ዓመታት እስከ አርባ ምንጭ ድረስ ዞሮ አስተምሯል፡፡

ቅዱስ ያሬድ

ቅዱስ ላልይበላ

ቅዱስ ላልይበላ ታህሳስ ፳፱ ቀን ፲፻፹ . ተወለደ፤ ሰኔ ፲፪ ቀን ፲፪፻፯ . አረፈ። በተወለደ ጊዜ በንብ ስለ ተከበበ እናቱ ማር ይበላል ለማለት "ላል ይበላል" ብላዋለች። ቅዱስ ላልይበላ የብሉያትንና የሐዲሳትን ትምህርት ትርጓሜ የተማረና ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው። ቅዱስ ላልይበላ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበረ ሲሆን፤ ስመ ንግስናውም አፄ ገብረ መስቀል ነበር። ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያሰራ ሲሆን በከተማው በደብረ ሮሃ ዓለምን ያስደነቁና ከታች የተዘረዘሩትን ¬፲፩ አብያተ ክርስቲያናትን በመላዕክት አጋዥነት ከቋጥኝ ፈልፍሎ ሠርቷል። . ቤተ አማኑኤል . ቤተ ገብርኤል . ቤተ መርቆሬዎስ . ቤተ መድሃኔዓለም . ቤተ መስቀል . ቤተ ሊባኖስ . ቤተ ማርያም . ቤተ ጎልጎታ ፲፩. ቤተ ደናግል . ቤተ ሚካኤል . ቤተ ጊዮርጊስ 

ቅዱስ ላልይበላ

ዘጠኙ ቅዱሳን

ዘጠኙ ቅዱሳን በኬልቄዶን ጉባኤ ምክንያት በተዋሕዶዎች ላይ በአውሮፓ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ በተነሣው ፈተና የተነሳ ከሮም፣ ከእስያ፣ ከአንጾኪያ፣ ከቁስጥንጥንያ፣ ከቂሳርያና ከኪልቂያ በስደት የመጡ ናቸው። ስማቸውም አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ ጰንጠሌዎን፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጵሕማ፣ አባ አፍጴ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ይምዓታ እና አባ ጉባ ይባላሉ። ዘጠኙ ቅዱሳን በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሲሆን በተለይም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጽንተዋል፣ የተለያዩ መጽሐፍትን ተርጉመዋል፣ ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል፣ በርካታ ገዳማትን መስርተዋል፣ ሥርዓተ ምንኩስናን አደራጅተዋል።

ዘጠኙ ቅዱሳን

አቡነ ተክለኃይማኖት

አቡነ ተክለኃይማኖት ታህሣሥ ፳፬ ቀን ፲፩፻፹፮ . በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ ተወልደው ነሐሴ ፳፬ ቀን ፲፪፻፹፮ . አርፈዋል። በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል። ኢትዮጵያን ዞረው ወንጌልን ከማስተማራቸውም በላይ ሕዝቡን ከባዕድ አምልኮ ወደ ክርስትና በመመለስ ይታወቃሉ። አቡነ ተክለኃይማኖት ክንፍ የተሰጣቸው ብቸኛው ጻድቅ ሲሆኑ በብርሃን ሠረገላ ይጓዙ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል። የግብጽ ክርስቲያኖች ለጻድቁ አባታችን ልዩ ፍቅር ያላቸው ሲሆን በስማቸው አብያተ ክርስቲያኖች ተክለዋል።

አቡነ ተክለኃይማኖት
ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት መስቀል ተአምራት ብዙዎች ከተለያየ ደዌ ተፈውሰዋል፡፡ይህም በጣም ብዙ ሰዎችን ክርስቶስን ወደ ማመን ስቧቸዋል፡፡ ይህን ድንቅ ስራ የተመለከቱ የክርስቶስ ጠላቶች መስቀሉ እውራንን በማብራት ደንቆሮዎች እንዲሰሙ በማስቻል ሽባ እየተረተረ ድንቅ ስራ መስራቱ ስላላስደሰታቸው መስቀሉን ከጎልጎታ አንስተው በግራና በቀኝ የተሰቀሉት ወንበዴዎች የተሰቀሉበትን መስቀል ለማሳሳት ጨምረው ቀብረውት ለ፫፻ ዓመታት ያህል የከተማው ጥራጊ ቆሻሻ እየተጣለበት የተቀበረበት ቦታ ተራራ እስኪሆን ድረስ ቆይቷል፡፡ ንግስት እሌኒ የመስቀሉ ፍቅር የነበራትና ለክርስትና ሃይማኖት የተገዛች ሃይማኖቷን የምትወድ ስለነበረች ልጇን የክርስትና እምነትን ትምህርት እያስተማረች ያሳደገች ቅድስት እናት ነች፡፡ ልጇ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ በዘመነ መንግስቱ በትእምርተ መስቀል ብዙ ጠላቶቹን ድል በመምታቱ የጦሩ ልዩ ምልክት አድርጎት ቆይቷል፤ ለመስቀሉ ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ነበረው፡፡ ንግስት እሌኒ የመስቀሉ ተቀብሮ መቅረት ሲያስጨንቃት ኑሯልና ሁኔታው ሲመቻች ፫፻፳፯ .. መስቀሉን ፈልጎ ለማግኘት ቆርጣ ተነሳች፡፡ነገር ግን ከዘመኑ ርቀት እንዲሁም ቦታው ሦስት ተራራዎች ያሉበትና በየትኛው ተራራ በእርግጠኝነት እንደተቀበረ የሚናገር ሰው ጠፋ፡፡ በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነበረና ትክክለኛ ቦታውን ለማግኘት ባደረገችው ያላሰለሰ ጥረት አባ ኪርያኮስ በተባለ ታላቅ መንፈሳዊ አባት ቦታው ከሶስቱ ተራራዎች በአንዱ መሆኑ ተነገራት፡፡በራእይም በተገለጸላት መሰረት ብዙ እንጨት አስደምራ ብዙ ዕጣን ጨምራ በእሳት በማያያዝ ሲቀጣጠል የእጣኑ ጢሰ ቅታሬ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ከወጣ በኋላ እንደ ቀስት ወደ መሬት ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አመልክቷል፡፡ በዚያውም ቦታ መስከረም ፲፯ ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት ቀን በተገኘ ጊዜ ታላቅ ደስታ ሆኗል፡፡እሌኒና ሠራዊቱ የመስቀሉን መገኘት በየሀገሩ ለመግለጽ ችቦ በማብራት ዜናውን አስተላልፈዋል፡፡ የሮም፣ የእስክንድርያ፣ የቁስጥንጥንያና የኤፌሶን ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ መስቀሉን በየሀገረ ስብከታቸው ለራሳቸው፣ ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው ኃይልና ጽንዕ በረከትና ረድኤት ሰላምና ፍቅር እንዲሰጣቸው ተካፍለው ወደየአህጉራቸው ሲወሰዱት ዋናውና መካከለኛው በኢየሩሳሌም እንደቀረ በአበው ይተረካል፡፡ የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው ጠንክሮ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር። ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊ ዓፄ ዳዊት እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግሥልን ብለው ጠየቁትዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶአቸው ሽህ ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብፅ ዘመቱ። በዚህ ጊዜ በግብፅ ያሉ ኃያላን ፈሩ ተሸበሩ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትምበተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋዋለሁየሚል ማስጠንቀቂያ ለእስላሞች ላኩ፡፡ የንጉሡ መልዕክት ለእስላሞቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደጥንቱ በየሃይማኖታቸው ፀንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡ ዐፄ ዳዊት በዋሉላቸው ውለታ ግብፆች ተደስተው ብዙ ወቄት ወርቅ እጅ መንሻ ቢሰጡአቸውም ወርቁን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉበግብፅ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝን ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፤ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም፤ የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ በኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው የሚል ነበር፡፡ በእስክንድርያም ያሉ ምእመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅድሳት ጋር አሁን በመለሰው ወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብር በሠረገላና በግመል አስጭነው ድንበር ድረስ አምጥተው አስረከቧቸው። ዐፄ ዳዊትም ክቡር መስቀሉን እንደተቀበሉ «አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀል ላይ አስቀምጥ» የሚል ራእይ ታያቸው፡፡ ንጉሡም ይህንን ትዕዛዝ በልባቸው ይዘው መስቀሉን ለአገራቸው ኢትዮጵያ በረከት እንዲሆንላቸው በደስታ ላይ እንዳሉ በጠረፍ አካባቢ እስከዛሬ ድረስ የዳዊት ተራራ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ላይ በድንገት ዐረፋ፡፡ በኋላ ግን ግማደ መስቀሉ ከክብር አጽማቸው ጋር በልጃቸው በዐፄ ይስሐቅ አማካኝነት መጥቷል። ዐፄ ይስሐቅም ከፍፃሜ ሳያደርሱት በሞት ስለተለዩ ወንድማቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ የአባታቸውን በትረ መንግሥት እንደጨበጡ በአደራ የቆየውን መስቀል ተረከቡ፡፡ «አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀል ላይ አስቀምጥ» የሚል ትእዛዛዊ ራእይ እንደ አባታቸው ስለታያቸው እንደሰንሰለት በተያያዙ በኢትዮጵያ ተራሮች ላይ በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አምባ ክቡር መሰቀሉን አኑረዋል፡፡

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም

በዚያም የእግዚአብሔር አብ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀው በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን መሠረት ውስጥ በተዘጋጀ ልዩ ቦታ መስቀሉን አስቀምጠው ቅዳሴ ቤቱን ነሐሴ ፲፫ ቀን የመስቀሉን ክብረ በዓል ደግሞ መስከረም ፳፩ ቀን፣ ፲፬፻፵፮ .. በድምቀት እንዲከበር ሲያደርጉ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ጥር ፳፩ ቀን ፲፱፻፵፱ .. ተከበረ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የመስቀሉና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀንና ጥር ፳፩ ቀን ብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ምእመናን በሚገኙበት በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡

ይቀጥላል፣ ይቆየን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር