ወቅታዊ ትምህርት

ወቅታዊ ትምህርት

የነቢያት ጾም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ፣ አሜን።

ጾመ ነቢያት ጾመ አዳም ጾመ ማርያም

በዘመነ ብሉይ ነቢያት እግዚአብሔር ወልድ ከንጽሕተ ንጹሐን፤ ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለአዳም የገባለትን ቃል ይፈጽም ዘንድ ትንቢት በመናገር ለሕዝቡ የምሥራችን ቃል ያበሥሩ ነበር፡፡… ነቢያቱ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው ሆኖ ዓለምን የሚያድንበትን ዘመነ ሥጋዌ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ የነቢያት ትንቢትና ጸሎትም በእግዚአብሔር ሰው መሆን ተፈጽሟል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ታሳቢ በማድረግ በዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ፤ ከኅዳር ፲፭ አስከ ታኅሣሥ ፳፱፤ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ እስከ ታኅሣሥ ፳፰ ጾም ታውጃለች፡፡

በዘመነ ብሉይ ነቢያት እግዚአብሔር ወልድ ከንጽሕተ ንጹሐን፤ ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለአዳም የገባለትን ቃል ይፈጽም ዘንድ  ትንቢት በመናገር ለሕዝቡ የምሥራችን ቃል ያበሥሩ ነበር፡፡ አምላካችን ከድንግል ተወልዶ ከእናቱ ጋር ወደ ግብፅ ምድር እንደሚሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል መከራና ስቃይ እንደሚቀበል፣ እንደሚሰቀል፣ እንደሚሞት፣ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፣ እንደሚያርግና ዳግም ለፍርድ እንደሚመጣ  በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው አስቀድመው ትንቢት ተናግረዋል፡፡

ነቢያቱም የትንቢቱን መፈጸም በተስፋ ይጠብቁ፣ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ይማጸኑ ነበር፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ‹‹ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣች‰ል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› በማለትም እንደተናገረ ትንቢት ኢሳይያስ ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ (ኢሳ. ፯፥ ፲፬)

እንዲሁም ነቢዩ ሚክያስም በቤተ ልሔም እንደሚወለድ እንዲህ በማለት ገልጿል፤ ‹‹አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተልሔም ሆይ! አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ከአንቺ ይወጣልኛል፡፡›› ሚክ. ፭፥፪)

ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላም ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ ግብፅ ሀገር እንደሚሰደድ እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት አናግሯል፡፡  ‹‹እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ እየበረረ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅም የእጆቻቸው ሥራዎች በፊቱ ይዋረዳሉ፤ የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል›› እንዲል፡፡ (ኢሳ.፲፱፥፩)

ነቢዩ ዳዊትም ‹‹ባሕር አየች፥ ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ‰ላው ተመለሰ፡፡ ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ በጎች ጠቦቶች ዘለሉ፡፡ አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንተም ዮርዳኖስ ወደ ‰ላህ የተመለስህ፟ ምን ሁናችሁ ነው?›› ብሎ እንደተናገረው ምሥጢረ ጥምቀቱ ይፈጸም ዘንድ የእግዚአብሔር አምላክ ፍቃዱ ሆነ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ በዮርዳኖስ ወንዝ እንደሚጠመቅ ቀድሞ ተነገረ፡፡ (መዝ. ፻፲፫፥፫)

ጌታችንም ከተጠመቀና ለትምህርተ ወንጌል በሚገለጥበት በ፴ ዓመቱ ለብዙዎች ትምህርተ ወንጌልን እንደሚሰብክ እና በጨለማ ውስጥ ላሉት ሕዝብም ሁሉ ብርሃን እንደሚወጣላቸውም የተስፋ ቃል ለሰው ልጅ ሁሉ ተነግሯል፡፡ ይህንንም ነቢዩ ኢሳይያስ ሲገልጽ፤ ‹‹በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው›› ብሏል፡፡ (ኢሳ. ፱፥፪)

ነቢዩም ጌታችን ስለ እኛ መከራ እንደሚቀበል ‹‹እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን›› በማለት አስቀድሞ እንደተናገረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧል፡፡

ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ሞትንም ድል አድርጎ እንደሚነሣ ‹‹እኔ ተኛሁ፤ አንቀላፋሁም፤ እግዚአብሔርም አንሥቶኛልና ተነሣሁ›› በማለት እንዲሁም ተነሥቶ እንደሚዐርግ ‹‹እግዚአብሔር በእልልታ÷ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ›› በማለት ነቢዩ ዳዊት ትንቢት ተናግbል፡፡ (ኢሳ. ፶፫፥፭፣መዝ.  ፫፥፭፣መዝ. ፵፮፥፭)

ይህ ይፈጸም ዘንድ ነቢያቱ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው ሆኖ ዓለምን የሚያድንበትን ዘመነ ሥጋዌ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ የነቢያት ትንቢትና ጸሎትም በእግዚአብሔር ሰው መሆን ተፈጽሟል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ታሳቢ በማድረግ በዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ፤ ከኅዳር ፲፭ አስከ ታኅሣሥ ፳፱፤  በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ እስከ ታኅሣሥ  ፳፰ ጾም ታውጃለች፡፡

ነቢያት የጾሙት ይህ ጾም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፤ ሁሉን ነገር በምክንያት የሚያደርገው አምላካችን እግዚአብሔር ለአዳም ድኅነት ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው የገባለት ቃል እንዲፈጸም ትንቢት በተነገረው መሠረት ነቢያት ቢጾሙት እና ‹‹የነቢያት ጾም (ጾም ነቢያት)›› ተብሎ ቢጠራም በመሰቀሉ የተቀበለለት መከራ ሁሉ የአዳምን እዳ ይከፍልለት ዘንድ ነውና ‹‹ጾመ አዳምም›› ይባላል፡፡

ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመሆኑም ‹‹የስብከት ጾም (ጾመ ስብከት)››የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመሆኑ ደግሞ ‹‹የልደት ጾም (ጾመ ልደት)›› በመባልም ይታወቃል፡፡

ይህ ጾም ‹‹የፊልጶስ ጾም (ጾመ ፊልጶስ)››ተብሎ ይጠራል፤ የዚህም ምክንያት ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ሁሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባኤ ይዘው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው ፈጣሪያቸውን በመማጸናቸው እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መለሰላቸው፤ ሥጋውንም (አስከሬኑን) በክብር ቀብረውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ድረስ ጾመዋል፤ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹የፊልጶስ ጾም (ጾመ ፊልጶስ)›› እየተባለ ይጠራል፡፡

በነቢያት ጾም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛም በዚህ ዘመን ከገባንበት ችግርና መከራ አምላካችን እግዚአብሔር ከፈተና እንዲያወጣን በጾም በጸሎት እንማጸን፤ ቸርነትንና ምሕረትንም እንለምን፡፡ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ የነቢያት ጾም ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡ – ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭

ጾምና ምጽዋት፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ – ፶፡፡

Read more