Holy Wedding

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናን ቅዱስ ጋብቻ

“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው” ዕብ ፲፫፡፬

ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም ጋብቻ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የምትረዳው ጓደኛ እንፍጠርለት ብሎ እግዚአብሔር ሔዋንን ከአዳም አካል ፈጠራት። ዘፍ ፪፡ ፲፰። አዳምም ከአካሉ የተፈጠረችውን ሰው አይቶ እንዲህ አለ፡ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ይህች ሥጋም ከስጋዬ ናት፤ እርሷ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።” ዘፍ ፪፡ ፳፫-፳፭። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በመልኩ ፈጠረ። ወንድና ሴትም አድርጎ ፈጠራቸው። ከዚያም እንዲህ ብሎ ባረካቸው፡ “ብዙ ተባዙም፣ ምድርንም ሙሏት፣ ግዟትም፣ የባህር አሦችና የሰማይ ወፎችን፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ግዟቸው።” ዘፍ ፩፡ ፳፮-፴፩።

ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ተገልጦ ወንጌለ መንግስትን እየሰበከ በዓለም ላይ በሚዘዋወርበት ወቅት ጋብቻ እጅግ የተቀደሰ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በተቀደሰ ጋብቻ አንድ የሆኑ ተጋቢዎች በመንፈሳዊ ሕይወት የተሳሰሩ አንድ አካል መሆናቸውን ገልጿል፤ “የገዛ ሚስቱን የወደደ ራሱን ይወዳል፣ ማንም የገዛ ስጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና” ሲል ባልና ሚስት አንድ አካል መሆናቸውን መስክሯል። ኤፌ ፭፡ ፳፩-፴፫። በሌላ መልእክቱም በሕገ ቤተክርስቲያን የተፈጸመ ጋብቻ ንጹሕና ክቡር መሆኑን አስተምሯል። ዕብ ፲፪፡ ፩-፮። ስለዚህ በሥርዓተ ተክሊል ማለት በቤተክርስቲያን ሥርዓት የሚፈጸም ጋብቻ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም የተባረከ በመሆኑ ሊፈርስ አይገባውም፤ “እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለየውም” ተብሎ የተሰጠው አምላካዊ ትእዛዝ ምንጊዜም መከበር አለበት። ማር ፲፡ ፩-፱። ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረው ማንም ሰው ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ቢፈታ እሷን አመንዝራ ወይም ዝሙት አዳሪ እንድትሆን ያደርጋታልና ሰውየው በደለኛ ይሆናል። ሴቲቱም ባልዋን ያለ ዝሙት ምክንያት ብትፈታውና ሰውየውም አመንዝራ ወይም ዘማዊ ቢሆን ለዚህ ኃጥያት ያበቃችው ሚስቱ ኃጥያተኛ ናት። ስለዚህ ባልና ሚስት ከኃጥያትና ከበደል ይድኑ ዘንድ በሕገ ቤተክርስቲያን አማካይነት የገቡትን የጋብቻ ቃል ኪዳን እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ጠብቀው መኖር ይገባቸዋል። በጋብቻቸው ጊዜ በእግዚአብሔር ስም በቤተክርስቲያን የገቡትን ቃል ኪዳን ማፍረስ ዐቢይ ኃጥያትና ትልቅ በደል መሆኑን ምን ጊዜም መርሳት አይገባቸውም።

የጋብቻ ዓላማ

የጋብቻ ዓላማዎች ሦስት ናቸው፡

1. የመጀመሪያውየሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለትእንዲል ለመረዳዳት ነው። መረዳዳት ሲባልም በሥጋ ብቻ አይደለም በነፍስም ጭምር ነው። ለሥጋቸው በሥራ ሲረዳዱ ለነፍሳችው ደግሞ በጸሎት ይረዳዳሉ። ለምሳሌ ይስሐቅ ሚስቱ ርብቃ ለሃያ ዓመታት መክና ልጅ አልወለደችለትም ነበር። በዚህም ምክንያት ስለ ርብቃ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፤ ርብቃም መንታ ፀነሰች ይላል። ዘፍ ፳፭፡ ፳፩።

2. ሁለተኛው ከፍትወተ ሥጋ ወይም ከዝሙት ለመጠበቅ። ፩ኛ ቆሮ ፯፡ - ፱፤ ፩ኛ ቆሮ ፭፡ ፩፤ ምሳሌ ፮፡ - ፴፪።

3. ሦስተኛው ደግሞ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸውብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏትእንዲል ዘር ለመተካት ነው። ዘፍ ፩፡ ፳፰። እነዚህም እንደ ሦስት ጉልቻዎች የሚቆጠሩ ናቸው።

ከመጀመሪያው ጋብቻ ምን እንማራለን?

አዳምና ሔዋን ወደዚህ ዓለም ከመምጣታቸው በፊት እግዚአብሔር በሥጋም በነፍስም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አዘጋጅቶላቸዋል። ከሁሉም በላይ በጸጋ አክብሮአቸዋል። ፍጥረታት ሁሉ ይታዘዙላቸውና ይገዙላቸው ነበር። እግዚአብሔር በልግስና ከሰጣቸው ሀብት በስተቀር በራሳቸው ያመጡት የራሳቸው የሆነ ምንም አልነበራቸውም። ሁለቱም ዕርቃናቸውን ነበሩ። ትልቁ ሀብት እግዚአብሔር በአርአያውና በመልኩ ፈጥሮ የሰጣቸው አካል ነው። አዳም በአርባ ቀኑ ሔዋንም በሰማ ንያ ቀኗ ወደ ገነት የገቡት ይህን አካላቸውን ይዘው ነው። ከገነት በተባረሩም ጊዜ ከአካላቸው በስተቀር ይዘውት የወጡት ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ጋብቻን በምናስብበት ጊዜ ሁሉን ነገር እግዚአብሔር የሚያዘጋጅ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። ለጋብቻ የመረጥነውም ሰው ዕራቁቱን ቢሆንም (ምንም ባይኖረው) እርሱነቱን ወይም እርሷነቷን ብቻ ለመቀበል መዘጋጀት አለብን። ወደዚህ ዓለም የመጣነው ዕርቃናችንን መሆኑን ለአፍታም መርሳት የለብንም። ዓለምን ጥለን የምንሄደውም ዕርቃናችንን ነው። ጻድቁ ኢዮብከእናቴ ማኅጸን ራቁቴን ወጥቻለሁ ራቁቴንም ወደ ምድር እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔር ነሣ፣ እግዚአብሔርም እንደፈቀደ ሆነ፣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁንያለው ለዚህ ነው። ኢዮ ፩፡ ፳፩።

ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ

ፈቃደ እግዚአብሔር የሚጠየቀው በጸሎት ነው። አዳም ከሐዘን ጋር የጸለየው በኅሊናው ነው። በመሆኑም ከልብ መጸለይ ያስፈልጋል።ፈቃድህ በሰማይ (በመላእክት ዘንድ) እንደሆነ እንዲሁም በምድር (በደቂቀ አዳም ዘንድ) ይሁንማለት ይገባል። ማቴ ፮፡ ፲። እንደ ፈቃዱም ስንለምነው ይሰማናል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስበእግዚአብሔር ዘንድ ያለችን መውደድ ይህች ናት፤ በስሙ ከእርሱ ዘንድ የምንለምነውን ይሰማናልና። የምንለምነውንም እንደሚሰማን ካወቅን እንግዲያስ በእርሱ ዘንድ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለንያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፭፡ ፲፬። ለምሳሌ ሁለት ማየት የተሳናቸው ሰዎች የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን እያሉ በእምነት በለመኑ ጊዜ፣እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰላቸው፣ ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ ይላል። ማቴ ፱፡ ፳፯። ጥሩ የትዳር ጓደኞችም እንደ ዓይን ናቸው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል የትዳር ጓደኛን በዓይን መስሎ ተናግሯል። ማቴ ፲፰፡ ፱። በተጨማሪም የሰውነት መብራት ዓይን እንደሆነ፣ ዓይን ብሩህ ከሆነ ሰውነት ሁሉ ብሩህ እንደሚሆን፣ ዓይን ግን ታማሚ ከሆነ ሰውነት ሁሉ ጨለማ እንደሚወርሰው ተናግሯል። ማቴ ፮፡ ፳፪። ስለዚህ ትዳራችን በውስጥ በአፍአ ብርሃን እንዲሆን ዓይን የሆነ የትዳር ጓደኛ እንዲሰጠን በእምነት ከለመንነው ይሰማናል። ልመናችንን እንደሰማን ካወቅንና ካመንን የለመንነውን ሁሉ በጊዜው ይሰጠናል።

የተክሊል ጋብቻ የሚገባው ለማን ነው?
  • ሥጋዊ ድንግልና ላላቸው
  • የሃይማኖት አንድነት ላላቸው
  • ለአቅመ አዳም ለደረሱ
  • ፈቃደኝነታቸውን ለገለጹ ተጋቢዎች

ጸሎተ ተክሊል ከቅዳሴ በፊት የሚፈጸም ሲሆን ያለሥጋ ወደሙም አይፈጸምም። የተክሊል ጋብቻን ለመፈጸም ሁለቱም ተጋቢዎች ድንግል መሆን ያለባቸው ሲሆን ነገር ግን ተጋቢዎቹ ከጋብቻ በፊት በግብረ ስጋ የሚተዋወቁ ከሆነ በተክሊል መጋባት አይችሉም። ሆኖም ግን በቤተክርስቲያንና በሥርዓተ ቁርባን ለመጋባት ምንም የሚያግዳቸው ነገር የለም፤ ንስሀ እስከገቡ ድረስ። ደናግላን ላልሆኑ ተጋቢዎች የሚደረገው ሥርዓት የመአስባን ጋብቻ ይባላል። ይህ ጋብቻ ከተክሊል ጋብቻ ሥርዓቱ የሚለይ ሲሆን በተክሊል እንደሚደረገውም ለተጋቢዎቹ በራሳቸው ላይ አክሊል አይደረግላቸውም። ይህ ለድንግልናቸው እንደመንፈሳዊ ሽልማት የሚሰጥ አክሊል ሲሆን ለመአስባን ተጋቢዎች ይህ አለመኖሩ ጋብቻቸውን የተቀደሰ ጋብቻ ከመሆን አያግደውም። እንዲያውም በትክክል እና ከልብ በመሆን ንስሀ ከገቡ መላእክት በስውር በአካለ ነፍሳቸው ራስ ላይ የድል አክሊልን ያቀዳጇቸዋል። ምክንያቱም ንስሀ የነፍስ ድንግልናን ታስመልሳለችና።

የተወደዳችሁ ምዕመናን ታዲያ ይህንን ሥርዓት ለመፈጸምና በሥርዓተ ተክሊል የሚገኘው መንፈሳዊ በረከት እንዳይቀርብን ከፈለግን እውነተኛ ንስሀ ያስፈልገናል። ያም ማለት ከጋብቻ በፊት በግብረ ስጋ መተዋወቃችን በፍጹም በቤተክርስቲያን ሥርዓት የማይደገፍ መሆኑን ተገንዝበን ከልብ በመጸጸት እግዚአብሔርን እንዳሳዘንን በማመን ንስሀ መግባት ይኖርብናል። ከንስሀ አባቶቻችን ጋር በመወያየት ከዚህ ውጭ የሰራነውንም ሌሎች ኃጢአታችንን በመናዘዝ ነፍሳችንን ፍጹም ንጹህ አድርገን ለጋብቻ መዘጋጀት ይኖርብናል። የሚሰጠንን ቀኖና (ለምሳሌ የጾም፣ የስግደት ወይም የምጽዋት ትእዛዝ) በሚገባ በመፈጸም ከእንባ ጋር የንስሀ ጸሎት ወደ ፈጣሪያችን በማቅረብ የነፍሳችንን ድንግልና ማስመለስ አለብን። ከዚያ በኋላ ነው ጋብቻችንን መፈጸም የሚኖርብን። ከተጋባንም በኋላ ከስጋ ወደሙ መራቅ የለብንም። ባመቸን ጊዜ ሁሉ በሰንበት ወይም በበዓላት ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ከትዳር አጋራችን ጋር መቀበል አለብን። ይህ ካልሆነ የጋብቻችን ዕለት ብቻ የተቀበልነው ስጋና ደሙ ለፈተና እንዳይዳርግን ልንጠነቀቅ ያሰፈልጋል። ምክንያቱም ሰይጣን ሁል ጊዜም ቢሆን ስጋውንና ደሙን የተቀበሉ ሰዎች ደግመው እንዳይቀበሉ ለማድረግ በጣም ይጥራልና ነው።

በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቅዱስ ጋብቻ እንዲፈጸምልዎ ጋብቻችሁን

ጋብቻችሁን በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ለመፈጸም የምታስቡ ምእመናን ከቤተክርስቲያኗ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ /ቤት ጋር በመገናኘት የበለጠ መረጃ ማግኘትና አስቀድማችሁ መርሀ ግብር ማስያዝ እንደምትችሉ እየገለጽን እግዚአብሔር አምላክ የተቀደሰ የጋብቻ በዓል እንዲያደርግላችሁ በመመኘትይትባረክ እንደ አብርሀምእያልን ቅዱስ ጋብቻችሁን እንዲባርክላችሁ ቤተክርስቲያን ትመኛለች።


ይህንቅጽሞልተውለሰበካመንፈሳዊአስተዳደርጉባኤጽ/ቤትከ 1 ሳምንትበፊትያስረክቡ!

ለአባልነትና ለቃልኪዳን ስጦታዎች