Church Faith

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን መሰረተ-እምነት

ኢትዮጵያ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲፈፀምባት የኖረች ጥንታዊት ሃገር ነች።በዘመነ-ሐዲስም ክርስትናን በመቀበል ቀደምት ናት። መጽሐፍ ቅዱስና ታሪካዊ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ኢትዮጵያ በሐዋርያት ዘመን ጥምቀተ ክርስትናን በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካይነት ተቀብላለች (የሐዋ 8÷26-36)። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ) በመጽሐፍ ቅዱስ እና በሱም ላይ በተመሰረቱት በሶስቱ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በኒቅያ (325 ዓ. ም.)፤ በቁስጥንጥንያ (481 ዓ.ም.) እና በኤፌሶን (431 ዓ.ም.) በተደነገጉት የሃይማኖት መግለጫዎች ላይ የተገነባ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ዋና ዋናዎቹን የቤተክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት መግለጫዎች በአጭሩ እናያለን።

የእግዚአብሔር መኖር

የማይታይና የማይመረመር ሁሉን ማድረግ የሚችል ሁሉን የፈጠረ መጀመሪያ ያልነበረው መጨረሻም የማይኖረው ለዘላለም የሚኖር አንድ አምላክ እግዚአብሔር መኖሩን እናምናለን። እርሱም ዘላለማዊ እና ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፤ ሁሉን ዐዋቂ እና በዓለም ሁሉ ምሉዕ ነው፤ ቅዱስ ጻድቅ እና ፍቅር ነው።

ምሥጢረ-ሥላሴ

እግዚአብሔር በባሕርይ በመለኮት በፈቃድ በሥልጣን አንድ ነው። ግን በስም በአካልና በግብር ሦስትነት አለው። የስም ሦስትነት፦ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ። የአካል ሦስትነት፦ አብ ፍፁም አካል አለው ወልድ ፍፁም አካል አለው እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስ ፍፁም አካል አለው። የግብር ሦስትነት፦ አብ ወላዲ አስራፂ ነው። ወልድ ተወላዲ ነው። መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ነው። በሦስቱ አካላት መቀዳደምና መበላለጥ የለም።

ሥነ-ፍጥረት

ይህ የሚታየው ዓለምና በውስጡ ያለው ሁሉ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ነው። ከዚህ ከሚታየው ዓለም ውጪም ሌላ የማይታይ ረቂቅ ዓለም በውስጡም ያሉት ረቂቃን ፍጥረታት አስቀድሞ ከነበረ ግብር ሳይሆን እምኀበ አልቦ በእግዚአብሔር ተፈጥረዋል። የፍጥረታት ዓላማ እግዚአብሔርን ማመስገን ሲሆን በተለይ ሰው ክብሩን ለመውረስ የተፈጠረ ነው። የተለያዩ ፍጥረታት (22) በስድስት ቀናት ተፈጥረዋል።

የእግዚአብሔር መግቦት

ዓለም በእግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ከመጣበት ዕለትና ሰዓት ጀምሮ በእግዚአብሔር መጋቢነት ሲመገብ በእግዚአብሔር ጠባቂነት ሲጠበቅ ይኖራል። እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረው ጀምሮ ለዐይን ቅፅበት እንኳ ተለይቶት አያውቅም። በልዩ ጥበቃ ይጠብቀዋል ይከባከበዋል እንዲሁም ይመግበዋል።

መላእክት

መላእክት በማይታየው ረቂቁ ዓለም የሚኖሩ ሲሆን ተፈጠሮአቸውም ከነፋስና ከእሳት ነው። ቁጠራቸው የማይወሰን እጅግ ብዙ ሲሆን ሥራቸውም ተልዕኮ ነው። ከእግዚአብሔር ወደ ሰዎች ለምሕረትም ለመዓትም ይላካሉ (ሉቃ 1÷19-26)፤ ባለማቋረጥ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፤ የቅዱሳንን ፀሎት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ (ራዕ 8÷3-4)፤ በችግር ጊዜ ይራዳሉ (የሐዋ 5÷19፤ 12÷7)፤ በፍርድ ቀን ከጌታ ጋር ይመጣሉ። በጠቅላላው በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል መልእክተኞች ሆነው ተልዕኳቸውን ይፈፅማሉ።

ሰይጣናት

መላእክት ሁላቸው መልካም ተፈጥሮታቸውን አልጠበቁም። ከእነርሱ አንዱ ዲያብሎስ በነፃ ፈቃዱ ወደ ክፋት አዘንብሎ በትዕቢቱ ወደ ሰይጣንነት ተለውጧል፤ በዘላለማዊ ፍርድም ወደ ጨለማ ተጥሏል። ሰይጣን ሁልጊዜ ሰዎችን ይፈትናል፤ ወደ ክፉ ይመራል፤ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲተላለፉ ያደርጋል።

የሰው ተፈጥሮና አወዳደቁ

በዚህ በሚታየው ግዙፍ ዓለም ውስጥ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ እጅግ የከበረና የፍጥረት ሁሉ አክሊል የሆነ ሰው ብቻ ነው፤ ሰው ሲባል ነፍስና ሥጋ ያሉት ነው። ሰው ረቂቅ ነፍስ ብትኖረውም መልአክ አይደለም፤ ግዙፍ አካል ቢኖረውም እንስሳ አይደለም፤ ከመልአክም ከእንስሳም የተለየ ነው። ሥጋዊና መዋቲ በመሆኑ ከመላእክት ይለያል፤ ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ ያለችው በመሆኑ ከእንስሳት ይለያል። የሰው ተፈጥሮ “ለይኩን” በሚል ቃል ሳይሆን በእግዚአብሔር እጅ በርሱ አርአያና ምሳሌ ነፃ ፈቃድ ያለው ሆኖ ተፈጥሯል። ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም ሰላይደለ እግዚአብሔር ከአዳም ጎን ሔዋንን ፈጠረለት፤ የሰው ዘር ሁሉ ከነዚህ ከሁለቱ ከአዳምና ሔዋን ተገኝቷል።

ሰው በተፈጥሮው ነፃ ፈቃድ ያለው ፍጥረት በመሆኑ በነፃ ፈቃዱ አመዛዝኖ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰይጣን መታዘዝን መረጠ። የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላለፈ፤ ይህም ኃጢአት ለዘሩ ሁሉ ተላለፈ። በኃጢአት ከወደቀና ከተረገመ ለሰይጣን ተገዥ ከሆነ በኋላ ወልዷቸዋልና ልጆቹ ሁሉ እንደርሱ ኃጢአተኞች ሆነዋል (ዘፍ 5÷3)። ሰው በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ከገነት ወጣ ልጅነቱን አጣ፤ ፀጋው ተገፈፈ። የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፉ ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ፤ ርደተ-መቃብርና ርደተ-ገሃነም ተፈረደበት (ዘፍ 3÷19፤ ሮሜ 6÷23)።

ምሥጢረ-ሥጋዌ

ሰው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላለፍ ፀጋው ተገፍፎ ከገነት ወጥቷል። ይሁን እንጂ በተፈጥሮ የተሰጠው ዕውቀቱና ነፃ ፈቃዱ ስላልተለየው እግዚአብሔር በፈታሒነቱ ቢፈርድበትም በመሐሪነቱ እንደሚምረው ስላወቀ በኃጢአቱ ተፀፀተ። እግዚአብሔርም ንስሐውን ተቀብሎ ከሰይጣን ባርነት ከኃጢአት ቁራኛነት ነፃ ያወጣው ዘንድ ፈቀደ። ስለዚህም “የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ” ጊዜ ከሶስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በፍፁም አካላዊና በሕርያዊ ተዋህዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ ተወለደ። ተወልዶም ከኃጢአት በቀር የሰውነትን ሠራ ሁሉ እየሠራ አደገ፤ በሰላሳ ዓመቱ ተጠመቀ፤ በጰንጤናዊው በጲለጦስ ዘመን ስለእኛ ታመመ ሞተ፤ ተቀበረ በሶስተኛውም ቀን ተነሣ፤ በ40ኛው ቀን ወደባሕርይ አባቱ በክብር አረገ፤ በተነሣ በ50ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ለደቀ መዛሙርቱ ላከላቸው።

ቃለ-እግዚአብሔር ወልድ ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምናለን። የመጀመሪያው ቅድመ-ዓለም ከአብ የተወለደው ሲሆን ሁለተኛው ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ያለ አባት የተወለደው ልደት ነው። አምላክ ሰው በሆነ ጊዜ ሰውም በተዋሕዶ አምላክ ሆነ። የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋም ገንዘብ ለቃል ሆነ። የቃል ገንዘብ ማለት አምላክነት የባሕርይ ምስጋና ቀዳማዊነት ገቢረ-ተዓምራት ሕያውነት ለሥጋ ገንዘቡ ሆነዋል። እንደዚሁም የሥጋ ገንዘብ ማለት ትሕትና ድካም መራብ መጠማት ሕማም ሞት እና ሌሎችም ለቃል ገንዘቡ ሆነዋል። እንደዚሁም ቅድመ-ዓለም ከአብ የተወለደው ቃለ-እግዚአብሔር ወልድ ድኅረ-ዓለም በሥጋ ወልደ ማርያም መባልን ገንዘብ አደረገ። ድኅረ-ዓለም ከእመቤታችን የተገኘው ሥጋም በቃል ወልደ አብ መባልን ገንዘብ አደረገ። ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋህዶ ከበረ።

የክርስቶስ ሕማም ሞት ትንሣኤና ዕርገት

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣቱ ስለ ዓለም ቤዛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎና ሞቶ ዓለምን ለማዳን ነው። ሞቱ ለበደላችን ሁሉ ካሳ (ቤዛ) ነው (ማቴ 20÷28)። ሞቱ ሞትን ደምስሶልናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞተ በሶስተኛው ቀን በመለኮታዊ ሥልጣኑ ተነስቷል። በክርስቶስ ትንሣኤ ሞትና ሰይጣን ድል ሆነዋል (1ቆሮ 15÷16፡ 20፤ ሮሜ 6÷3- 11፤ ኤፌ 2÷4-6)። የሰው ልጅ ድኀነት ተፈፅሟል (ሮሜ 4፤25)፤ የርሱ ትንሣኤ የኛን ትንሣኤ ያረጋግጥልናል፤ እርሱ በክብር እንደተነሣ እኛም እንደሱ በክብር እንነሳለን (1ቆሮ 15÷20-22)። ትንሣኤው ለክርስትና እምነት መሠረት ነው (1ቆሮ 15÷17-18)። ጌታችን ከተነሳ በኋላ በአርባኛው ቀን በክብር ወደ ሰማይ አረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ ይህም የአድኅኖቱ ሥራ ፍፃሜ ነው።

ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ

ድንግል ማርያም ከቤተ-ዳዊት የተወለደች ናት። በ15 ዓመት እድሜዋ በብሥራተ-መልአክ በግብረ-መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወለደች። ቅድስት ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት፤ ከመፅነስ በፊት በመፅነስ ጊዜ እና ከመፅነስ በኋላም ድንግል ናት። ከመውለድ በፊት በመውለድ ጊዜ እና ከመውለድ በኋላም ድንግል ናት። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሐሳብም በቃልም በግብርም ኃጢአት የሌለባት ፍፅምት ንፅሕት ናት። ይሁን እንጂ እመቤታችን ከኢያቄምና ከሐና በሩካቤ ዘበሕግ የተገኘች ናት እንጂ ከሰማይ የወረደች የመላእክት ወገን አይደለችም፤ ካሳ የማያስፈልጋትም ሳትሆን ክርስቶስ በደሙ ከዋጃቸው ካሣም ከተከፈለላቸው ወገን ናት። ንፅሕት ቅድስት ማርያም ክብር ምስጋና የሚገባት ናት። መላእክትም ሰዎችም አክብረዋታል አመስግነዋታል (ሉቃ 1÷28-29፤ ሉቃ 1÷40-42)። ድንግል ማርያም እመ-አምላክ ወይም ወላዲተ-አምላክ ተብላ ትጠራለች (ሉቃ 1÷32)። እርስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ከፍተኛ ባለሙዋል ስለሆነች አማላጃችን ናት፤ እርስዋ ለእኛ የአደራ እናታችን ናት፤ እኛም ለእርሷ የአደራ ልጆች ነን (ዮሐ 19÷27-29) ስለዚህ ትማልድልናለች። እመቤታችን በ64 ዓመት እድሜዋ አዳማዊ ሞትን ሞታለች ይሁን እንጂ ሙስና መቃብር አላገኛትም፤ በሞተች በሶስተኛው ቀን በእግዚአብሔር ኃይል ተነስታ በክብር አርጋለች።

ትንሣኤ ሙታን የክርስቶስ ዳግም ምፅአትና የመጨረሻው ፍርድ

የዚህ ዓለም ፍፃሜ በሚሆንበት ጊዜ የሙታን ትንሣኤ፤ የክርስቶስ ዳግም ምፅአት፤ የመጨረሻው ፍርድና የዘላለም ሕይወት በተከታታይ ይፈፀማሉ። ሞት የሰው ፍፃሜ አይደለም ከጊዜያዊ ሕይወት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ ነው እንጂ። ዛሬ ፈርሶ በስብሶ ዐፈር ሆኖ ያለው የሰው ሥጋ ከነፍስ ጋር ተዋሕዶ ይነሣል። ከትንሳኤ በኋላ ሰዎች ሁሉ እንደመላእክት ይኖራሉ (ማቴ 22÷30)። ትንሳኤ ሙታን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ ይሆናል፤ ከትንሳኤ ሙታን ቀጥሎ ወዲያው ጌታችን ይመጣና የመጨረሻ ፍርድ ይሰጣል፤ ከዚያም የዓለም ፍፃሜ ይሆናል። ቀድሞ ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ በትሕትና መጥቶ የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም ፍጻሜ ጊዜ ዳግመኛ በክብር ይመጣል። የሚመጣበት ዓመትና ወር ዕለትና ሰዓት ፈፅሞ አይታወቅም። ዳግመኛ የመምጣቱ ዓላማ “በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ” ይሆናል። በክርስቶስ ዳግም ምፅአት ጊዜ ሞት ይጠፋል፤ ሰይጣንም ለዘላለም ይታሠራል፤ ሕይወት ብቻ ለዘላለም ይቀጥላል (1ቆሮ 15÷51-57፤ ዕብ 2÷14፤ ራዕ 20÷10-15፤ ራዕ 22÷12)። ከላይ የዘረዘርናቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ መሠረተ-ሃይማኖት ዋና ዋና መግለጫዎች ቀጥሎ በሰፈረውና ጸሎተ-ሃይማኖት እየተባለ በሚጠራው የእምነት መግለጫ ይጠቃለላሉ።

ምሥጢራተ-ቤተ-ክርስቲያን

ምሥጢራተ-ቤተ-ክርስቲያን በክርስቶስ ክርሰቲያን ለተባሉ ሰዎቸ በቻ የሚሰጡ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ፀጋን ረቂቅ ሀብትን የሚሰጡ ናቸው። በዚህም የተነሳ ምስጢራት ተብለዋል። ምሥጢራተ-ቤተ-ክርስቲያን በክርስቶስ መሥራችነት የተመሰረቱ፤ ክርስቶስ ራሱ በዕለተ ዓርብ ካደረገው የማዳን ሥራ የመነጩ፤ የማዳን ሥራውም ያለማቋረጥ እስከ ዓለም ኅልፈት እየቀጠለ የሚሄድባቸው፤ ኃይሉ የሚታወቅባቸው ሥልጣኑ የሚገለጥባቸው የማንፃትና የማፅናት ሥራው የሚቀጥልባቸው ታላላቅ ምሥጢሮች ናቸው። ምሥጢራተ-ቤተ-ክርስቲያን ቁጥራቸው ሰባት ነው። እነሱም ምሥጢረ ጥምቀተ፤ ምሥጢረ ሜሮን፤ ምሥጢረ ቁርባን፤ ምሥጢረ ንስሐ፤ ምሥጢረ ክህነት ምሥጢረ ተክሊል እና ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው።